የኮሌጁ ታሪክ | History of KPC
ሀገራዊ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ስትራቴጂ በግልፅ እንዳስቀመጠው የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ዋና ዓላማ በሀገሪቱ እየተካሄደ ያለውን ኢኮኖሚያዊ እድገትና ማህበራዊ ልማት መደገፍ የሚችል ብቁ፣ ተፎካካሪና ተወዳዳሪ የሆነ በመካከለኛ ደረጃ የሰለጠነ የሰው ኃይል በማፍራት ለሥራ ገበያው/ ለኢንዱስትሪው ማቅረብና የማኅብረሰቡን የኑሮ ደረጃ በማሻሻል ድህነትን ለዘለቄታው መቀነስ ነው፡፡ በመካከለኛ ደረጃ የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት ደግሞ የቴክኒክና ሙያ ተቋማትና ኮሌጆች የአንበሳውን ድርሻ ይይዛሉ።
የአማራ ክልላዊ መንግስት መዲና ከሆነችው ከባህር ዳር በስተምስራቅ በኩል በ500 ኪሎ ሜትርና ከፌደራል መንግስቱ መቀመጫ ከአዲስ አበባ ደግሞ በ377 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው የምስራቅ አማራ የኢንዱስትሪ ኮሪደር በሆነችው ኮምቦልቻ ከተማ ላይ የተንጣለለውን የቦርከና ወንዝ ተንተርሶ የተገነባው የኮምቦልቻ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት ተምሳሌት ከመሆኑም አልፎ በአንስተኛና መካከለኛ ደረጃ የሰለጠነ ብቁ እና ተወዳዳሪ የሰው ሃይል ለማፍራት ትኩረት ሰጥቶ በመስራት የክልሉን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ልማት በመደገፍ በኩል ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።
የኮሌጁን ታሪካዊ አመሰራረት በሶስት ምዕራፎች ከፍሎ ማየት ይቻላል። የመጀመሪያው ምዕራፍ በአመሰራረቱ ላይ የሚያጠነጥን ሲሆን ኮሌጁ በ 1994 ዓ. ም. የኮምቦልቻ ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋም በሚል ስያሜ በዛሬው የኮምቦልቻ አጠቃላይ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ ተመስርቶ በኮንስትራክሽን የስልጠና ዘርፍ በሰርትፍኬት ደረጃ (በ10+1) የአጫጭር ስልጠና በመስጠት ሥራውን ጀመረ፡፡ በዚሁ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሥራ እንደጀመረ የሚነገርለት የኮምቦልቻ ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋም ከትምህርት ቤቱ በመገንጠል ለብቻው ተለይቶ ዛሬ የቦርከና ካምፓስ በሚባለው ቦታ ላይ በ10+2 የስልጠና መርሃ ግብርም ስልጠና መስጠቱን ቀጠለ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ መንግስት በመላ ሀገሪቱ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ለማስፋፋት ባለው ፅኑ ፍላጎት የተነሳ በኢንዱስትሪዋ መንደር በሆነችው የኮምቦልቻ ከተማ ውስጥ በቴክኖሎጂና ኢንዱስትሪል ዘርፎች ስልጠና የሚሰጥ ኮሌጅ መክፈት አስፈላጊ መሆኑን ተረዳ፡፡ በመሆኑም በፌደራል ትምህርት ሚኒስቴር በጀት የግንባታ ሥራው እንደተጀመረ የሚነገርለት የኮምቦልቻ ኢንዱስትሪያል ቴክኖሎጂ ኮሌጅ ግንባታ በመካሄድ ላይ እያለ በክልሉ መንግስት ምክር ቤት አዋጅ ቁጥር 12/1995 ተቋቁሞ ቀደም ሲል ከተመሰረተው የኮምቦልቻ ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋም ጋር በቦርከና ከምፖስ በመዳለብ መደበኛ ሥራውን በ 1996 ጀመረ፡፡ ኢንዱስትሪያል ቴክኖሎጂ ኮሌጁ በቦርከና ካምፓስ ውስጥ ሥራውን የጀመረው በ6 የስልጠና ዘርፎች ማለትም በኤሌክትሪሲቲ፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ አውቶሞቲቭ፣ ጀኔራል መካኒክስ፣ ማሽን ቴክኖሎጂና ቴክስታይል ቴክኖሎጂ በአጠቃላይ 150 ተማሪዎችን ተቀብሎ በ10+3 ፕሮግራም ስልጠና በመስጠት ነበር።
ሁለተኛው ምዕራፍ የሚባለው ደግሞ በአንድ ግቢ ውስጥ የማሰልጠኛ ቤት እየተጋሩ በራሳቸው የሰው ኃይልና ማቴሪያል ስልጠና ሲሰጡ የነበሩት የኮምቦልቻ ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋምና የኮምቦልቻ ኢንዱስትሪያል ቴክኖሎጂ ኮሌጅ ከ2000 ዓ.ም. ጀምሮ በመዋሃድና አንድ በመሆን የኮምቦልቻ ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኮሌጅ በሚል ስያሜ የተቀየረበትን ጊዜ ነው። የኮምቦልቻ ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኮሌጅ ውህደቱ የፈጠረለትን የሰው ኃይልና የማሰልጠኛ ቁሳቁስ እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም የስልጠና ዘርፎቹንና መስኮቹን በማስፋት በመደበኛ፣ በማታና በአጫጭር ጊዜ ስልጠናዎች በርካታ ወጣቶችን እየተቀበለ በሁለት ካምፓሶቹ (ቦርከና እና ሼህ ሸቢር ካምፓሶች) ስልጠና በመስጠት የሙያ ባለቤት ሲያደርግ ቆይቷል፡፡
በሦስተኛው ምእራፍ ላይ ኮሌጁ በማሰልጠኛ ቁሳቁስ አደረጃጀት የስልጠና አቅሙን በማጠናከሩና በማስፋቱ በሰው ኃይልና አደረጃጀቱ የተሻለ ለመሆን ከጊዜ ወደ ጊዜ ባደረገው ጥረት ከመጋቢት 2007 ጀምሮ የኮምቦልቻ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ በመባል የስምና የደረጃ ለውጥ በማድረግ እስከ ደረጃ አምስት ባሉ የብቃት ደረጃዎች ስልጠና መስጠት ጀመረ፡፡ ከመጋቢት 2008 ጀምሮ ደግሞ የሳተላይት ተቋም በመሆን በማኑፋክቸሪንግ፤ ኤሌክትሪካል ኤሌክትሮኒክስ፤ በአውቶሞቲቭ ቴክኖሎጂ የስልጠና ዘርፎች በድግሪ መርሀ ግብር ስልጠና የጀመረበትን ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ኮሌጁ ከላይ በተጠቀሱት የስልጠና ዘርፎች በመደበኛ፣ በማታና በተከታታይ ትምህርት በድግሪ መርሀ ግብር ስልጠና እየሰጠ ይገኛል፡
ኮሌጁ የሚሰጠዉን የቴክኒክና ሙያ ስልጠና እና የቴክኖሎጂ ሽግግር ተግባራት ዓለም አቀፋዊ ደረጃቸዉን የጠበቀ ለማድረግና የክልሉን ብሎም የሀገሪቱን ስትራቴጂያዊ አላማዎች ለማሳካት ያስችል ዘንድ በ 2009 ዓ.ም የ ISO 9001:2008 የጥራት ሥራ አመራር ስርዐትን ተግባራዊ ለማድረግ በርካታ ሥራዎችን ሲያከናውን ቆይቶ ከኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ የዓለም አቀፍ የጥራት አስተዳደር ስርዓት (Quality Management System) እውቅና ምስክር ወረቀት አግኝቷል። በአሁኑ ጊዜ ደግሞ ወደ ISO 9001:2015 የጥራት አስተዳደር ስርዓት (Quality Management System) ስርዐት ቨርዢን በመሸጋገር ቀልጣፋ፣ ጥራቱን የጠበቀ ፣ ደንበኛ ተኮር፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆነ ኮሌጅ ለመሆን የሚያስችል የምስክር ወረቀት አግኝቷል። የስልጠና ጥራትን በተጨባጭ ለማረጋገጥና የደንበኞችን እርካታ ክፍ ማድረግ የሚያስችለውን የጥራት አስተዳደር ስርዓት (ISO 9001:2015) ከመተግበር ጎን ለጎን የጥራትና ምርታማነት አሠራርን ቀጣይነት ባለው መልኩ የሚያሻሽል የካይዘን ስርዐትን ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ በማድረግ ያለማቋረጥ ቀጣይነት ባለው መልኩ ማስቀጠልም ሌላኛው የኮሌጁ ዋና ተግባር ነው፡፡
Kombolcha Polytechnic College: A Brief Historical Overview As outlined in Ethiopia’s National Technical and Vocational Education and Training (TVET) Strategy, the core goal of TVET is to produce skilled, qualified, and competitive professionals who can drive the nation’s economic growth and social development. Technical and vocational colleges like Kombolcha Polytechnic College (KPC) play a vital role in building this capable workforce and helping reduce poverty through practical, industry-focused education and training. KPC is located along the Borkena River in Kombolcha, the industrial hub of East Amhara—about 500 km from Bahir Dar and 377 km from Addis Ababa. The college has become one of the region’s leading centers for technical and vocational training, contributing significantly to the local and national economy by producing competent middle-level professionals. The college’s story unfolds in three key phases. It began in 2001 as Kombolcha Technical and Vocational Education and Training Institute (KTVETI), initially offering short-term construction training at the certificate level (10+1). Soon after, it expanded into a 10+2 program at what is now the Borkena Campus. Responding to the government’s initiative to strengthen industrial and technology education, Kombolcha Industrial Technology College (KITC) was founded in 1996 by Regional Proclamation No. 12/1995, under the Federal Ministry of Education’s budget. KITC later merged with KTVETI, enrolling 150 students in six training sectors, including Electricity, Electronics, Automotive, General Mechanics, Machine Technology, and Textile Technology. In 2007, the two institutions united to form Kombolcha Technical and Vocational Education and Training College, creating new opportunities to expand training programs. With improved resources and manpower, the college began offering regular, evening, and short-term courses across its two campuses—Borkena and Sheikh Sabir. A new chapter began in March 2014, when the college was restructured and renamed Kombolcha Polytechnic College. It upgraded its training capacity to offer Level Five programs and, since 2016, degree-level courses in Manufacturing, Electrical and Electronics, and Automotive Technology. Today, KPC continues to train students through regular, evening, and continuing education programs. Committed to global quality standards, the college adopted the ISO 9001:2008 Quality Management System in 2009, earning international certification from the Ethiopian Standards Agency. It later upgraded to ISO 9001:2015, reaffirming its status as an efficient, quality-driven, and customer-focused institution. Alongside ISO implementation, KPC has also embraced the Kaizen system, promoting a culture of continuous improvement, productivity, and excellence.